ኢትዮጲያዊ

ኢትዮጲያ ለምን ደሃ ሆነች?

ድህነት እጅግ አስከፊ ስለመሆኑ ለእኛ ለኢትዮጲያውያን ሊነገረን የሚገባ ነው ብዩ አላስብም፡፡ ኢትዮጲያ በብዙ የድህነት ደማቅ ታሪኮች ያለፈች አገር ናት፡፡

በእዚህ አነስተኛ ጽሁፍ ውስጥ የተወሰኑ ሃሳቦችን ለመወርወር እፈልጋለሁ፡፡ አንባቢው የእራሱን እይታ ቢያክልበት አይከፋም ባይ ነኝ፡፡

1999 ዓ.ም ነበር፤ ለኢትዮጲያ ሚሊኒየም መግቢያ ዋዜማ ላይ በወቅቱ እጮኛዬ አሁን ሚስቴ ና የልጄ የኤልባርክ እናት የሆነችውን ሰላማዊት በቀለን “እስኪ ስለ ኢትዮጲያ ያለፉት 2000 ዓመታት ጉዞ በወረቀት የሰፈረውን ለማንበብ እንሞክር አልኮት…” አላማዬ የኢትዮጲያን ያለፉት 2000 ዓ.ም ጉዞ በታሪክ አዋቂዎች እይታ እንደተቀመጠው መረዳት ነበር፡፡ መጽሃፍትን ሰበሰብን … አነበብን… አነስተኛ ማስታወሻም እንዲሆን ወደ ወረቀት በመመለስ ለማጠናከር ሞከርን … ከእዚያ በላይ መጎዝ ሳንችል ቀረና … ጽሁፉ እኛው ዘንድ ቀረ…

የ 2000 አመታት የኢትዮጲያ ጉዞ ውስጥ ከደመቁት እውነታዎች መካከል አንዱ ና ዋነኛው እርስበርስ አለመስማማት እንደሆነ ተረዳሁ፡፡ አለመስማማት፣ መጋጨት፣ ጦር መማዘዝ፣ እርስበርስ መተላለቅ … አቤት የፈሰሰው ደም … አቤት የባከነው ትውልድ … አቤት የባከነው ንብረት … አቤት በአለም አቀፍ ደረጃ የተናደው ስማችን…

እኛ ኢትዮጲያውያን አንድ ትልቅ የቤት ስራ አለብን፡፡ እናት የወለደችውን ልጅ ይዛ መንገድ ዳር ማየት ለእኛ የተለመደ ነው፡፡ ሰው በርሃብ ሲቃ ውስጥ ደራሽ አጥቶ እስከወዲያኛው ሲያሸለብ ለማየት ጥቂት ወራት በኢትዮጲያ ውስጥ መንቀሳቀስ በቂ ነው፡፡ የእለት ተእለት ኑሮን ለመምራት እናቶች ጎብጠው ሲሄዱ ለማየት በየትኛውም የኢትዮጲያ መንገዶች ላይ ብቅ ማለት ብቻውን በቂ ነው፡፡ ….

አሁን ጥያቄው ኢትዮጲያ ለምን ደሃ ሆነች ነው? ከመነሻው እንዳልኩት በመካከላችን ያለው እራስ ወዳድነት ነው፡፡ ሀገራዊ እይታ አለመያዛችን ነው፡፡ አንድነታችን የሚሰጠንን ክብር አሻግረን አለመመልከታችን ነው፡፡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ማለታችን ነው፡፡

እርግጥ ያለፈው ትውልድ አልፉል፡፡ ያለፈው ትውልድ መልካም አደረገ ክፉ ላይመለስ አልፉል፡፡ አሁን ጥያቄው ሊሆን የሚገባው በእዚህ ትውልድ ላይ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ከትላንት ይልቅ “የተማረ የሰው ሃይል” በሚለው ስም ለመጠራት የበቃ ትውልድ … ይህ ትውልድ በትላላቅ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች ስለ ብዙ አለም አቀፍ ጉዳዮች የሚወያየው ትውልድ … ይህ ትውልድ ከሚያገኘው 100 ብር 101 ብሩን እራሱ ላይ የሚያውለው … ይህ ትውልድ ስለ እንግሊዝ ፕሪሜርሊግ ከ ሀ እስከ ፐ የሚተነትነው … ይህ ትውልድ ስለ ሆሊውድ ተዋንያን ውሎና አዳር እያስበ ውሎ አስቦ የሚያድረው …

በኢትዮጲያ ውስጥ በርከት ያሉ ምናልባትም በመላው አለምውስጥ አሉ የሚባሉ የግብረሰናይ ድርጅቶች አሉ፡፡ እኒህ ግብረሰናይ ድርጅቶች ገንዘባቸውን አንዳች ለውጥን ፍለጋ በኢትዮጲያ ላይ ያፈሳሉ፡፡ የፈሰሰው ጠብታ መለኪያው ቢያስችግርም በቁጥር ስብጥር የሚቀመጠው የገንዘቡ ብዛት ኢትዮጲያን የአለም ባንክ ሊያስብላት ይችላል፡፡ እኒህ ለጋሾች የሚሰጡን ገንዘብ በአግባቡ ለሃገሪቱ በተቀናጀ ሁኔታ የደረሳት አይመስለም፡፡ እኔነት የወረሰን ስለሆነን … እኛው ባንዳዎች መሰልን፡፡ አየ ኢትዮጲያ…. ተስፋሽ የት የሆን? አምናለሁ ከላይ ነው፡፡

ከልጅነቴ የክረምት ወራት በአንዱ … አባቴ ስራ ፈለጋ ከእኛ እራቅ ብሎ ሄዶል፡፡ እናቴ፣ እኔናወንድሜ አብረን እንኖራለን፡፡ ከክረምቱ በአንዱ ቀን የእናቴ ትግል ተረታ … ምንም ልታበላን የምትችለው ነገር እጇላይ አለቀ፡፡ ጠራችኝና “… ልጄ አንተ ከፉንና ደጉን ታውቃለህ እስኪ እንማከር አሁን የማበላችሁ የለኝም፡፡ አንድ ነገር ብቻነው ማድረግ የምንችለው እርሱም ክረምቱ ካበቀላቸው ቅጠላ ቅጠሎች ወስደን ቀቅለን እንበላለን… ወንድምህንም ጎመን ነው እንለዋለን” አለችኝ … እናቴ እንዳደረገችው አደረግን .. ጎመን ያይደለውን ጎመን ነው ብለን በላን … ክረምቱም አለፈ … እኛ አልሞትንም…

ስለ እርሃብ ለማያውቅ ሰው በርሃብ ስለመሞት ማስረዳት ከባድ ነው፡፡ እናስብ… ምናልባት ዛሬ ባለማስተዋል የምንወስነው ውሳኔ፣ የምንራመደው እርምጃ፣ ነገ ሌሎች ወደ ሞት እንዲሄዱ ምክንያት ይሆናቸው ይሆናል …

እርምጃን እንውስድ ባለንበት በማናቸውም ቦታ በርሃብ ሰው የማይሞትባትን ኢትዮጲያን ለማግኘት እንስራ፡፡

ፓለቲካ የአመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ የተለያዩ አመለካከቶች መኖራቸው በአግባቡ ከተመራ ለሃገር እንደሚጠቅም አስባለሁ፡፡ የትኛውም ፓለቲካዊ አመለካከት ግን መስዋእትነትን ሊጠይቅ ይገባዋል፡፡ ለሕዝብ የማሰብ መስዋእትነትን፣ ለጊዜ ዋጋ ሰጥቶ ለሀገር ፈውስ የማሰብ ደግሞም የማድረግን መስዋእትነትን፡፡

የቀለም እውቀት መያዝ የሁላችንም ጥረት ነው፡፡ ምሩቅ የሚያሰኝ ወረቀት ከመያዝ ባሻገር እውቀትን ለሰዎች መልካም ኑሮ መኖር መለወጥ ትክክለኛ አዋቂነት ነው፡፡ ኢትዮጲያ አንቱ ለመባል በወረቀት ላይ ወረቀትን የሚጨምሩ፣ የተሻለ ተከፋይ ለመሆን የ Scholarship በሮችን ደጋግመው የሚያንኳኩ ሰዎችን አትፈልግም፣ ኢትዮጲያ ሁላችንን በመቻቻል በረሃብ ምክንያት ከመሞት እንድንወጣ ትፈልጋለች፡፡

በሕይወት ዘምኔ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሚከተሉት ሀገራት ተወላጆች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አውርቼአለሁ፡፡ ከ ፈረንሳዊ፣ ኪንያዊ፣ ቦትስዎናዊ፣ ሞዛምቢካዊ፣ኮሪያዊ፣አሜሪካዊ፣ግብጻዊ እና እንግሊዛዊ፡፡ ሁሉም ለሃገራቸው መልካም እይታ እንዳላቸው ተረዳሁ…. ስለ እራሴ፣ ስለ ጎደኞቼ፣ስለ… አስብኩና አዘንኩ

ኢትዮጲያ በድህነት እንዳትቀጥል … ኢትዮጲያ ሰው በርሃብ የሚሞትበት ሃገር እንዳትሆን … ኢትዮጲያ በእግዚአብሔር የተባረከች ሃገር እንድትሆን ሁላችንም እግዚአብሔርን እንጠይቅ … በውሳኔዎቻችን ሁሉ ውስጥ ሀገራችንን፣ህዝባችንን እንመልከት … እንማር ግን ለምን እንደምንማር እናስብ … በፓለቲካ ውስጥ የምትሳተፉ ተሳተፉ ግን ለመላው ኢትዮጲያውያን ጥቅም እንጂ ለግላዊ እንዲሁም ለቡድናዊ ጥቅም አትኑሩ … ትዳር ይኑረን ግን ቤተሰባዊ ሕይወትን በመጠበቅ ነገላይ መንገድ ዳር የሚወጡ እናቶች እንዳይኖሩ እናስብ … ልጆች ይኑሩን ግን አሜሪካንን ሳይሆን ኢትዮጲያን እያሳየን እናሳድጋቸው፡፡

ለዛሬ እዚህ ላይ ይብቃኝ … ከስጋ፣ከነፍስእና ከመንፈስ እግዚአብሔር በእራሱ አምሳል የሰራው የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ነው … ኢትዮጲያ ለምን ደሃ ሆነች?

ሐብታሙ ኪታባ

Advertisements

Comments on: "ኢትዮጲያ ለምን ደሃ ሆነች?" (1)

  1. God bless you for the wonderful idea and inspiration. While I was a freshman student I remember a philosopher who said “….an unexamined life is not worth living”. You know these days it seems we don’t have time for introspection.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

Tag Cloud

%d bloggers like this: