ኢትዮጲያዊ

ከ አንድ አመት በፊት…

በእዚህ ጽሁፍ ጥቂት የማደንቃቸውን አስደናቂ በሚል መጠሪያ ልጠራቸው የወደድኩትን ሰዎች ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡ እኔህ ሰዎችን በተደጋጋሚ አስባቸው የነበረው የዛሬ አንድ አመት ገደማ ነበር፡፡ ተራ በተራ እያሰብኩ ስደነቅባቸው… ስለ እነርሱ ለሌሎች ሳወራ ነበር፡፡ ዛሬ ግን በወረቀት ላይ በጥቂት ፊደላት ልገልጻቸው ፈለኩ፡፡ የተደነቁት በእኔ ብቻ አይመስለኝም … በታላቁ መጽሐፍ ተድነቀዋልና ማድነቄ የበረታ ነው፡፡

ወቅቱ…

ወቅቱ አለማችን ከታእምራት በላይ የሆነውን ታእምራት የሆነውን ታእምራት ያስተናገደችበት ወቅት ነበር፡፡ አምላክ በሰው አምሳል የተወለደበት ወቅት፡፡ አምላክ ሁሉን መሆን እንደሚችል በተግባር ያሳየበት ወቅት፡፡ ይህንን ወቅት ቁልጭ አድርጎ የሚያስራዳው መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ ስለማነሳቸው አስደናቂ ሰዎች በቂ የሆነ መረጃን አስፍሮ አንብቤያለሁ…

ከማን ልጀምር…?

አሁን አንባቢው እኒህን ሰዎችን እያሰባቸው ይሆናል፡፡ የጽሁፉ ርእስ “በሁለት ኪዳናት መካከል የነበሩ አስደናቂ ሰዎች” ስለሚል ሰዎች ላይ ማተኮሬ እሙን ነው፡፡ እኒህ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፣ ሁሉም በስማቸው እከሌ ና እከሊት ተብለው እልተጠሩም፣ … በጥቅል ስም የተጠሩ ቢኖሩም፣ በግል ስም የተጠሩም አሉም… እኒህ ሰዎች ወንድም እንዲሁም ሴትም አለባቸው፣ ወጣት፣አዛውንትም አለባቸው… ታዲያ ከማን ልጀምር… በእድሜ ደረጃ ከመሄድ በሰዎች ዘንድ ካላቸው ታዋቂነት አንጻር እኔ እንደማስበው ተራበተራ ልመለከታቸው አስብኩ….

በታዋቂነት ደረጃ ላስቀምጣቸውና ተራ በተራ ከህይወታቸው ውስጥ አድንቆትን እንድሰጣቸው ያደረገኝን የሕይወት ዘመን ጉዞ አሻራቸውን ላስቀምጥ፡፡ እነርሱም እኒህ ናቸው ማርያም (የኢየሱስ እናት)፣ ዩሴፍ (የማርያም እጮኛ)፣ ዩሐንስ (መጥምቁ)፣ ስምኦን (ካህኑ)፣ ዘካርያስ (የዩሐንስ አባት)፣ ኤልሳቤጥ (የዩሐንስ እናት)፣ ሐና (ነቢይቱ)፣ እርኞች፣ ሰብአ ሰገል…

ሁሉንም በጥልቅት ለመመልከት አላሰብኩም፡፡ አንዳንዶቹን ሰፋ፣ አንዳንዶቹን ደግሞ ጠበብ አድርጌ ልተርካቸው አስባለሁ፡፡ ብዙ አስደናቂ እውነታዎችን ስላገኘሁባቸው አስደናቂ ልላቸው ወደደኩ፡፡ በእዚህ ዘመን ኖረው ጎደኞቼ ቢሆኑ ወይንም ቤተሰቦቼ ቢሆኑም አሰብኩ፡፡ እውነት ነው በእዚህ ዘመን የእኒህን ጀግኖች ፈለግ የተከተሉም አሉ … ምንም እንኮ በአቅራቢያዬ ብዙ ባይኖሩም…

የተረት መጽሐፍት እና ልብ-ወለዶች …

ሰዎቹ ምእራብዊ ሚስዮናዊ ናቸው፡፡ ስማቸውን ዘነጋሁት፡፡ ኢትዮጲያ ውስጥ ስለነበራቸው የሚስዮናዊ አገልግሎት በጻፉት መጻፈቻው ላይ ያሰፈሩትን አነበብኩ፡፡ በሚስዮናዊ አገልግሎታቸው ካላቸው ትውስታዎች መካከል አንዱ ለአንዲት እናት ወንጌልን ሲነርጉ የእናትየዎ ምላሽ ነበር፡፡ ሚስዩናዊው ወንጌልን ይነግራሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ እንደሞተ… እርሱን የሚያምኑ ከአጋንንት ነጻ እንደሚወጡ… ከሞቱ በኃላ ከፈጣሪ ጋር እንደሚኖሩ …ሌላም ሌላም…፡፡  ወንጌልን በመስማት ላይ ያሉት ሴት ፊት ላይ የሚነበበውን ነገር ሚስዮናዊው ሲገልጹ … አንዴ የሴትየዎ ፊት ይብራል፣ መልሶ ደግሞ ይደብዝዛል … ብለዋል፡፡ ጸሃፊው የሴትየዎ ፊት መቀያየር ምክንያቱን ለማወቅ ፈለጉ፡፡ ምክንያት ሆኖ የተገኘው የሴትዩዎ ደስታናስጋት መቀላቀሉ ነበር፡፡ ደስታቸው አዳኝ እንዳለ፣ ከአጋንንት ሚጠብቃቸው ሌላ የበላይ እንዳለ መስማታቸው እርሱን በማመን እረፍትን የማግኘት ተስፋቸው ነበር፡፡ ስጋታቸው የሚባለው ነገር በተልምዶ ይሰሙዎቸው የነበሩት የቀድሞ ተረቶች እና የፈጠራ ታሪኮች መካከል አንዱ እንዳይሆንባቸው ነበር፡፡ ደስ አላቸው አዳኝ ስላለ … ሰጉ እንደ ሌሎች ተረቶች ተረት እንዳይሆን ብለው… ፡፡ በእዚህ ምክንያት ፊታቸው አንዴ ፈካ አንዴ ጨለም አለ፡፡

እጅግ መሳጭ ፊልም እየተመለከቱ ምናልባትም በታሪኩ ሃዘን ይሰማዎት ይሆናል፡፡ በእዚህ መሃል የፈጠራ ጽሁፍ መሆኑን ሲያውቁ መለስተኛ እረፍት የሰማዎታል፡፡ የፈጠራ ታሪክ ስለሆነ፡፡ በእውነተኛ ታሪኮች ላይ የተመሰረተ ፊልምን ሲያዩ ግን ሃዘንዎት ወደ ትክክለኛ ሃዘን ይጠጋ ይሆናል…

አድንቆትን የሰጠኃቸው እኒህ በሁለት ኪዳናት መካከል የነበሩት ሰዎች የፈጠራ ሰዎች አይደሉም፡፡ እንደ እኔና እንደ አንባቢው ሰዎች ነበሩ፡፡ ሰው ሆነው የተወለዱ፣ ሰው ሆነው በወቅቱ ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ያለፉ፣ ሰው ሆነው የደከሙ፣ ሰው ሆነው ያዘኑ እንዲሁም የተደሰቱ፣ ሰው ሆነው የሞቱ… ያለፉ፡፡

የተረት መጽሐፍት እና ልብ – ወለዶች በደራሲው የሚፈጠሩ ሰዎች እንዳሉ ያስገነዝቡናል፡፡ እኒህ ሰዎች ግን የደራሲ ፍጡሮች ሳይሆኑ የእግዚአብሔር አምባሳደሮች ነበሩ፡፡ ነበሩ… አልፈዋልና! ግን ልንማርባቸው ይገባናል… ከማለፋችን በፊት ትርጉም ባለው ነገር ልናልፍ ይገባናልና…፡፡

በእዚህኛው ጽሁፌ የኢየሱስን እናት ማርያምን አስነብባለሁ

ማርያም (የኢየሱስ እናት)

ወጣቶቹ በእኔው የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ስለ እጮኝነት፣ስለ ትዳር እንዲሁም ስለ ሌሎች ተጎዳኝ ጉዳዮች እየተጫወትን ነው፡፡ እኔም እጮኛ እንዳለችኝ፣ በጣም እንደምወዳት፣ እርሷን ከማግባት ወደኃላ የሚያስብል ምንም ምክንያት እንደሌለኝ ተናገርኩ፡፡ ጨዋታችን እየሰፋ ሄደና በአሁን ዘመን ድንግል የሆነች ሴት በተለይም በከተሞች አከባቢ ማግኘት አስቸጋሪ ነው የሚል ሃሳብ ተነስቶ የተለያዩ ሃሳቦች መቅረብ ጀመሩ፡፡ ሃሳቡን ያቀረበው ወጣት በአብዛኛው ድጋፍ አግኝቷል፡፡ እኔ ግን ስለ እጮኛዬ ድንግል መሆን አንዳች ታክል ጥርጥር እንደሌለኝ ተናገርኩ፡፡ ተሳቀ፡፡ አትሞኝ፣… በምን አወቅክ አሉኝ…. ለማስረዳት ሞከርኩ… አልተስማማንም…

ከተለያየን በኃላ አሰብኩ፡፡ እኒህ የእድሜ እኩዮቼ ሃሳብ በአብዛኛው ተቀባይነት ያለው ይመስለኛል፡፡ እውነታዋን በአብዛኛው በሚል ቀዳሚ ተቀጽላ ከመቀበል ውጪ እጮኛዬ ላይ ልጠቀምበት አልደፈርኩም፡፡ … ጊዜ ይፍታው አልኩ … ጊዜም ፈታው እጮኛዬን በድንግልናዋ የእኔ ሆነች …

ግን የድንግልና መዳረሻ የቱ ጋር ነው፡፡ ግብረስጋ ግንኙነት አለማድረግ ብቻውን ድንግል ያስብል ይሆን? በፍጹም! የከናፍርት ግንኙነት … የድንግልና ማጫ ዋዜማ ነው….!

ይህ የጾታዊ ስሜት ፈተና የሰው ልጆች ፈተና ሆኖ የተጠቀሰው በዘመነ ግሎባላይዜሽን አይደለም፡፡ ገና ያኔ ከዘፍጥረት … አደጋው ተጠቅሶል፡፡ የሰዶምና ገሞራ ጥፋት፣ የብርቱው ታጋይ ሳምሶን ውድቀት፣ የንጉስ ዳዊት ስህተት፣ የምድረበዳው የእስራኤላውያን እልቂት … ድሮ የተከሰተ ታሪክ ነው፡፡

ይህ ፈተና የሰው ልጆች ሁሉ የተፈተኑበት ፈተና ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ ይህ ፈተና አሁንም አለማችንን ቀዳሚ ፈተና ሆኖ እየመራ ያለ ፈተና ነው፡፡ ይህ ፈተና የቤተ-ክርስቲያንን በር እያንኮኮ ያለ ፈተና ነው፡፡ ይህ ፈተና የአለማችን የአንድነት ሃብት የሆነውን የመረጃ መረብ እየረበሸ ያለ ፈተና ነው፡፡

ፈተናውን በድል የተወጡ … ስሜታቸውን የገዙ ሰዎችም የእግዚአብሔር ቅሬታ መሆናቸውን በጭካኔያቸው ያሳዩበት አንዱ መድረክ ነው፡፡ ዩሴፍ ያእቆብ… የያእቆብ ልጅ ዮሴፍ በሽሽት አመለጠው …

እግዚአብሔር ለሰውልጆች ብሎ ያዘጋጀውን የመዳን መንገድ ወደ ምድር ለማውረድ በተነሳ ጊዜ አሻግሮ ወደ ምድር ተመለከተ፡፡ ከሴቶች ሁሉ በቅድስና የተለየች ድንግልን ተመለከተ፡፡ ታላቅ የሆነው የእግዚአብሔር ሃሳብ በእዚች ሴት በኩል እንዲያልፍ ወሰነ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም በእርሷ በኩል እንዲወለድ የምስራች ይነግራት ዘንድ መላኩ ገብርኤል ተላከ፡፡ መላኩ ገብርኤልም የምስራቹን ነገራት… ይቺ ሴት ኢየሱስን የወለድችው ቅድስት ማርያም ነበረች፡፡

ማርያም በሁለት ኪዳናት መካከል የነበረች ሴት ናት፡፡ በብሉይ እና በሃዲስ፡፡ በአሮጌው እና በአዱሱ፡፡ በጥላው እና በዋናው፡፡ በጊዜያዊው እና በዘላለማዊው፡፡

ይህ ትውለድ… ጸሃፊውእና አንባቢው ከቅድስት ማርያም ህይወት ምን ይማራል ብለን ብናስብ የምናገኘው መልስ ደማቅ ይሆናል

    ከማርያም ለቅድስና ቅድሚያ መስጠትን እንማራለን

እግዚአብሔር በዘመናት መካከል የሚሰራው ስራ አለው፡፡ በአብርሃም ዘመን የነበረውን ስራ በአብርሃም እና በሌሎች ወገኖች በኩል ሰራ፡፡ በዳዊት ዘመን የነበረውን ስራ በዳዊት እና በወቅቱ በነበሩት ወገኖች ሰራ፡፡ በኤርምያስ ዘመን የነበረውን ስራ በኤርምያስ እና በሌሎች ወገኖች ሰራ፡፡ በዳንኤል ዘመን የነበረውን ስራ በዳኔኤል እና በሌሎች ወገኖች ሰራ፡፡ እንዲሁም በማርያም ዘመን የነበረውን ሥራ በማርያምእና በሌሎች ወገኖች ሰራ፡፡ እግዚአብሔር በእዚህ ዘመን ሊሰራ የሚያስበውን ሥራ የሚሰራባቸው ሰዎች ምንኛ የተባረኩ ናቸው፡፡ ከእነርሱ መካከል እሆን ዘንድ እሻለሁ፡፡ ለቅድስና ቅድሚያ የሰጡ… ለእግዚአብሔር ሃሳብ እራሳቸውን የለዩ… ምናምንቴን ነገር የማይደባልቁ እነርሱ የእግዚአብሔር ገንዘቦች ናቸው፤ ማርያም በዘመኗ የእግዚአብሔርን ሥራ እንደሰራችው…

ከማርያም ለእግዚአብሔር ሃሳብ መታዘዝን እንማራለን

መላኩ ቅዱስ ገብርኤል የምስራቹን ቃል በነገራት ጊዜ “…እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ…” በማለት ተቀበለች፡፡

ያለ ትዳር አርግዞ መገኘት በሚያስወግርበት ሃገር … ለእግዚአበሔር ሃሳብ ለመገዛት እራሶን አስጨከነች፡፡ ድንቅ ሴት ነበረች፡፡

መላኩ ገብርኤል የምስራች ይዞ ወደ መጥምቁ ዩሐንስ አባት ዘካርያስ ዘንድ በሄደ ጊዜ ዘካርያስ ለማመን ቸገረው፡፡ ስለአለማመኑም ዲዳ ሆነ፡፡ መናገር አቃተው፡፡ ማርያም ግን ለማመን ደግሞም ለመቀበል ቆረጠች …

የእግዚአብሔርን ቃል የማመን አቅማችን ምን ያህል እንደሆነ እራሳችን እንመዘን፡፡ እርግጥ ነው … ቃሉን ቀንበቀን እንሰበካለን… እርግጥነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን እናነብ ይሆናል … ግን እምነታችን ምን ያህል ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ለሕይወታችን ያለውን ሃሳቡን ተቀብለን፣ አመነን እንድንኖርበት የመንጨክነው ስንቶቻችን እንሆን?

የእግዚአብሔርን ቃል በማመን እና በእግዚአብሔር ቃል በመኖር እግዚአብሔር በእዚህ ዘመን እየሰራ ባለው ስራ ተካፋዮች እንሆናለን፡፡

ዛሬ የወንጌልን ቃል ለሰው ልጆች ሊያደርሱ የወጡ ደስ ይበላቸው … እነርሱ እግዚአብሔር በእዚህ ዘመን እየሰራ ያለው ሥራ ተካፋዮች ሆነዋልና፡፡ የእዚህ ሥራ ተካፋዮች ለመሆን ቃሉን ማምን… ቃሉን ማመን… በቃሉ መኖር ግድ ይላል፡፡ በክርስቶስ እና በወንጌሉ ቃሉ የምናፍር ወዮልን በአብ ፊት ወልድ ያፍርብናልና፡፡ ወልድን ክርስቶስን በልባችን ዙፋን ላይ በወጉ ያላስቀመጥን ወዮልን መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር አይደለምና፡፡

ሰው ወንጌልን ሰምቶ የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን ክርስቶስን አምኖ ሲኖር መንፈስ ቅዱስን ይቀበላል፡፡ ምንፈስ ቅዱስ … ቅዱስ ነውና ቀድሞ የተቀደሰ ስፍራን ይፈልጋል፡፡ ክርስቶስን በማመን የኃጢአቱን ስርየት ያገኘ … በእግዚአብሔር ቃል ቀን በቀን በመኖር በቅድስና የተገኘ ሰው እርሱ መንፈስ ቅዱስን የማግኘት ሙሉ መብት አለው፡፡

ማርያም የመጣወን የእግዚአብሔርን ሃሳብ በማመን እና በመቀበሏ እንደ ዘካርያስ ዲዳ ከመሆን ዳነች … ለእኛም እንማርባት ዘንድ ምክንያት ሆነች፡፡ የእግዚአብሔር ቃል … የእግዚአብሔር ቃል …. የእግዚአብሔር ቃል …. ምን ያህል በልባችን ውስጥ ይሰማናል? ምንያህልስ እርምጃችን በእዚህ ቃል ይገለጻል …

ከማርያም ስለ ማህበራዊ ሕይወት መፍትሄነት እንማራለን

የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ለመጻፍ እግዚአብሔር የተጠቀመባቸው አራት ሰዎች ናቸው፡፡ ከአራቱ ሁለቱ ሐዋርያት ሲሆኑ፣ ሁለቱ ደግሞ የኢየሱስ ተከታይ ከነበሩት ሰዎች መካከል የተቆጠሩ ናችው፡፡ ማቲዎስ እና ዩሐንስ ሐዋርያት ሲሆኑ ማርቆስ እና ሉቃስ ከሌሎች የእዚያን ወቅት የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች መካከል የተቆጠሩት ናቸው፡፡ ከሐዋርያት የወንጌል ጸሃፊዎች መካከል ዩሐንስ አንዱ ነው፡፡ በእግዚአብሔር መንፈስ ማነሳሳት እና እርዳታ ዩሐንስ በጻፈው የወንጌል  ቃል ሁለተኛው ምእራፍ ውስጥ ማርያም ስለተገኘችበት የሰርግ ስነስርአት እናነባለን፡፡

በእዚህ የሰርግ ቦታ ለሰርጉ የተዘጋጀው የወይን ጠጅ የታደመው እድምተኛ ስላልተጣጣመ የወይን ጠጁ ሁሉን በወጉ ሳይስተናገድ አለቀ፡፡

ዩሐንስ እንዲህ ሲል ይህን ሁኔታ ይገልጸዋል “በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው።” ዩሐንስ 2፡1-2

ማርያም ለሁኔታው መፍትሄ መመልከት ጀመረች፡፡ ወደ ኢየሱስ አየች፡፡ የወይን ጠጅ የላቸውም አለችው፡፡ እስኪ ቆም ብለን እናስብ፡፡ ማርያም የወይን ጠጅ ማለቁን ለምን ለኢየሱስ መንገር አስፈለጋት? ለእኔ የገባኝ ምክንያት ኢየሱስን በደንብ እንደምታውቀው ያስገነዝበኛል፡፡ አንዳች ታምራት ማድረግ እንደሚችል አውቃለች፡፡ ስለእዚህ ኢየሱስን ጠየቀችው፡፡ ምናልባት በእዚያ ቅጽበት ሁኔታውን ያስተዋሉ ማለትም የወይንጠጅ ማለቁን ያወቁ የሰርጉ እድምተኞች እያሽሟጠጡ ይሆናል፡፡ ማርያም ግን በኢየሱስ ውስጥ ያለውን መለኮታዊ አቅም ተርዳታለችና ነገረችው፡፡

ዛሬም በዙሪያችን ያለውን ማህበራዊ ሁናቴ ስንመለከት በርካታ ምስቅልቅሉ የወጣ የማህበራዊ ሕይወት ቀውሶችን እናያለን፡፡ ማርያም ኢየሱስን የጠየቀችበት የሰርግ ስንስርአት ማህበራዊ ቀውስ አድርገን የምንወስደው አይደለም፡፡ ዛሬ እጅግ የከፈ ቀውስ ውስጥ አለን፡፡ በፓለቲካው፣ በማህበራዊ ረገድ፣ በንግድ ስርአቱ፣ በቤተ-ክርስቲያን እንዲሁም በአራቱም አቅጣጫ የፈራረሰ በርካታ ጉዳይ አለ፡፡ መፍትሄው አንድ ነው … መፍትሄው ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ ዛሬ እኔናአንባቢው በእራሳችን ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን በአግባቡ ብንሾም ለማህበራዊ ቀውስ አባባሾች ከመሆን በዳን ነበር፡፡

ማርያም ጠንካራ የሆነ ማህበራዊ ሕይወት ከመኖሯ ባሻገር ሰዎች ለተቸገሩበት ነገር ኢየሱስን ታማክረው ነበር፡፡ ዛሬም ኢየሱስ ክርስቶስን ብንጠራው ይሰማናል … ቤታችንን ማሳመር ይችላል …ሕይወታችን ሕይወት … ሕይወት እንዲሸት ማድረግ ይችላል፡፡

 

ከማርያም ከወገኖች ጋር ሕብረት ስለማድረግ እንማራለን

30 አመታት ሳይገለጥ ኖረ … 3 አመታት አገለገል … በ33ኛው አመቱ ሞተ…ተቀበረ…ተነሳ…ወደ ሰማይ አረገ… ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያርግበት ጊዜ የደቀመዛሙርቱን ስሜት ምን እንደነበር ለማወቅ የምንቸገር ይመስለኛል፡፡ ግርታው መኖሩ ግን አጠያያቂ አይደለም፡፡ ከእርገቱ በፊት ደጋግሞ እየተገለጠ እንደተናገራቸው የወንጌል ጸሃፍት በአግባቡ ዘግበውታል፡፡

ሙያው ሕክምና እንደነበር የሚነገርልት ሉቃስ ነበር የሉቃስ ወንጌልን እና የሐዋርያትን ሥራ መጽሃፍት እንዲያዘጋጅ እግዚአብሔር የተጠቀመበት፡፡ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ በመጀመሪያው ምእራፍ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኃላ የሆነውን ሲጽፍ… ሐዋርያት ሥራ 1፡1-14

1-2 ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ኢየሱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ካዘዛቸው በኋላ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ፥ ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ ስለ ጀመረው ሁሉ መጀመሪያውን ነገር ጻፍሁ፤

3 ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው።

4 ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን። ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤

5 ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ።

6 እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት።

7 እርሱም። አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤

8 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።

9 ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።

10 እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤

11 ደግሞም። የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።

12 በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።

13 በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም።

14 እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።

ወቅቱ እየሩሳሌም በአዳዲስ ክስተቶች የተሞላችበት ወቅት ነበር፡፡ በተለይ ለኢየሱስ ተከታዮች ሁኔታው ህልም…ህልም ይመስላቸው ይሆናል፡፡ እኔ በእዚያን ዘመን በእዚያ ቦታ ሆኜ ብሆን ብለን ብናስብ ምናልባት ሁኔታዎችን በተሻለ ሁኔታ እንረዳው ይሆናል፡፡ እስኪ ሐዋርያው ጲጥሮስን ሆነን ለማሰብ እንሞክር፡፡ ኢየሱስን ተከተለ … ስለ ሞቱ ሲናገር ሰማው …አይሆንብህ አለው… ኢየሱስም ገሰጸው… የመጨረሻው ጽዋውን የሚጠጣበት ጊዜ እንደቀረበች እንዲሁም ሁሉም እንደሚተውት ሲናገር ሰማው … ጴጥሮስ ግን ሁሉ ቢተውህ እኔ ግን አልተውህም አለው … ኢየሱስም ለጴጥሮስ እንደሚክደው በምልክት ነገረው … ሁሉም ሆነ … ጴጥሮስም ካደው … ኢየሱስም በአደባባይ ተሰቅሎ ሞተ … ሁሉም ተበተኑ … በሦስተኛው ቀን የመነሳቱ ዜና ተሰማ … ጴጥሩስ ወደ መቃብሩ ስፍራ ሮጠ… ኢየሱስ በመቃብሩ የለም … ተሰብስበው ሳሉ … ሰላም ለእናንተ ይሁን በማለት ኢየሱስ በተዘጋው በር ገብቶ በመካከላቸው ሆነ …

አስብ/ቢ… ጴጥሮስ በእዚህ ሁሉውስጥ ምን ይሰማው ይሆን … ነገሮች ሁሉ ህልም፣ቅዥት… ምትሃት ወይስ ድራማ ይመስለው ይሆን? … ይህ ሁሉ ሆነ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሊያርግ ተነሳ … ተከታዮቹም ሸኙት … እኒህ ጀግና የእግዚአብሔር አገልጋዮች ኢየሱስ ክርስቶስ አይናቸው እያያቸው ወደ ሰማይ ሲያርግ ተመለከቱ … ከአይናቸው እስኪሰወር በአይናቸው ሸኙት … ኢየሱስ አረገ … አሁን በሁሉም ውስጥ አንድ ጥያቄ ሊኖር ይችላል ሕይወት እንዴት ይቀጠላል? ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ጸሎት ጀመሩ ከእነርሱም መካከል የኢየሱስ እናት ማርያም አብራ ነበረች፡፡ አብረው ጸለዩ… ቀናትን በጸሎት እና በሕብረት አሳለፉ … መንፈስቅዱስ መጣ … ቤተ-ክርስቲያን ተወለደች…

ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ መሰረትነት እንድትወለድ እግዚአብሔር ባሰበው ወራት የሥራው ተካፋይ ከሆኑት ሰዎች መካከል ማርያም አንዷ ነበረች …፡፡

ከወገኖች ጋር ሕብረት በማድረግ ማለትም በጸሎት እና በቃሉ ትጋት የእግዚአብሔር የጊዜው ሃሳቡ ይፈጸማል፡፡ ዛሬ የእግዚአብሔር ሃሳብ ሰዎች በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኙ፤ ከዘላለም ፍርድ እንዲወጡ ነው፡፡ ማርያም ከወገኖች ጋር ሆና ትጸልይ ነበር፡፡ ዛሬም ከወገኖች ጋር ሕብረት በማድረግ ለእኛ ዘመን የተወሰነውን የእግዚአብሔርን ሃሳብ ልናገለግል ይገባናል፡፡ ይህንንም ከማርያም እንማራለ፡፡

ይህን ጽሁፍ ለመቋጨት ልሞክር፡፡ የመነሻ ርእሴ በሁለት ኪዳናት መካከል የነበሩ አስደናቂ ሰዎችን ማንሳት ነው፡፡ ከእኒህ አስደናቂ ሰዎች የሕይወት ጉዞ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስቀምጥለን እውነታዎች ተነስተን መማር፡፡ ወናው የጽሑፉ አላማ ታሪክን ማወቅ ሳይሆን ከእኒህ ሰዎች መማር ነው፡፡ በእዚህ በመጀመሪያው ገለጻ ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ የተወለደባትን ማርያምን ተመልክተናል፡፡ ከማርያም ሕይወት

  1. ለቅድስና ቅድሚያ መስጠትን
  2. ለእግዚአብሐር ሐሳብ መታዘዝን
  3. ለማህበራዊ ሆነ ለሌሎች ችግሮች ለኢየሱስ መንገርን
  4. ከወገኖች ጋር በጸሎት በመሆን የእግዚአብሔርን ሃሳብ በአንድነት ማገልገልን ተምረናል፡፡

በቀጣይ ጽሁፍ እስከምንገናኝ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን

ሐብታሙ ኪታባ  

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

Tag Cloud

%d bloggers like this: