ኢትዮጲያዊ

ዘወትር በአዲስ አበባዋ ሜክሲኮ ባለፍኩ ቁጥር ስለ ሰው ልጅ በቁጥር መብዛት አስባለሁ፡፡ ወደ ሜክሲኮ ብቅ ያለ ሰው የሚመለከተው የሰው ግርግር እና የመኪናው ትርምስ አለም ሁሉ ሜክሲኮ የተሰበሰበ ያስመስለዋል፡፡

አንድ ቀን በትርምስ ውስጥ ያለውን ሰው ፊት ለማየት ፈለኩ ከታክሲ መቆሚያ ጥግ ጋር ቆሜ የእያንዳንዱን ሰው ፊት ለማየት ሞከርኩ፡፡ በአሁን ሰአት ይህ ሰው ምን ያስባል፣ በአሁን ሰአት እቺ ሰው ምን ታስባለች በሚል ጥያቄ የሰዎችን ፊት ለማየት ሞከርኩ፡፡ አንዳንዱ ከመቸኮሉ የተነሳ የመኪና ጎማን ከቁቡ ሳይቆጥር ከመኪና ጋር ትከሻ ለተከሻ ይተሻሻል፣ አንዳንዱ እጅግ በተመስጦ ሃሳብ በሚመስል ሁኔታ በዙሪያው ያለውን ሁሉ እረስቶ ወደ ጉዳዮ ይፈጥናል፣ አንዳንዱ ፊቱን ከስክሶ ይጎዛል፣ አንዳንዱ በቡድን እያወራ ያልፋል፣ አንዳንዱ ከንፈሩን እያንቀሳቀስ ከእራሱ ጋር እየተማከረ ያልፋል፣ አንዳንዱ የቀጠረውን ሰው ለማየት ዙሪያ ገባውን ይቃኛል… በመሃል ሜክሲኮ…

በእዚህ ሁሉ ግርግር መሃል፣ አንድ ነገር አሰብኩ፣ አሁን እንደው ማን ይሞት ከእዚህ ሁሉ ሰው ስንቱ ይሆን ከሞት በኃላ ስላለው ህይወት የሚያስብ፣ እንደ ፈጣሪ ምሪት ለመመላለስ የሚጨክን፣ የዘላለሙ ጉዳይ የሚያሳስበው ስለ ጠይኩ፡፡ እኔም ከእራሴ ጋር እያወራሁ ነውና ከንፈሬን ሳላንቀሳቀስ የቀረሁ አይመስለኝም፡፡ መልሼ አሰብኩ፣ አሁን እኔ አንዱን ሰው ጠጋ ብዬ ወንጌል ልነግረው ባስብ የሚሰማኝ ይኖር ስል ደግሞ አሰብኩ፡፡ በፍጹም በእዚህ ግርግር መሃል ማንም አይሰማኝም ስል መልሼ ለራሴ አወራሁ፡፡ ግን ወዲያው የአንድ ቀን ገጠመኝ ትዝ አለኝ፡፡ አንድ ቀን ከ ቄራ መስመር ወደ ሜክሲኮ እየተራመድኩ… መቼስ እየነዳሁ ለማለት መኪና ያስፈልጋል… አዋ እየተራመድኩ አንዴት ወጣት አንድን ሰው ወንጌልን እየነገረች ወደ ሜክሲኮ ሲሄዱ አይሁ፣ እኔም ወንጌልን ሰምቼአለሁ፣ በአቀራረቦም ተመስጬአለሁ፡፡ ስለዚህ በእዚህ ግርታ ውስጥ ሰዎች ወንጌልን ሊሰሙ ይፈቅዳሉ ማለት ነው፡፡ ግን አይመስለም፣ ምክንያቱም ሰው ፊቱን አኮሳትሩ ሲባትል አስፈሪ ስለሚመስል፡፡

የሆነው ሆኖ ሃሳቤን ቀጥልኩ በእርግጥ አዎ ሰዎች ኑሮ ሲከብዳቸው፣ እምነታቸውን ሲሰረቅ፣ ከዙሪያቸው ካሉት ያነሱ ሲመስላቸው፣ አንድን ነገር ለመያዝ ሲጥሩ … ብዙ ሊመሰጡ… ብዙ ከእራሳቸው ጋር ብቻ ሊሆኑ… ብዙ ፊታቸውን ሊያኮሳትሩ … ብዙ ዙሪያቸውን ሊረሱ ይችላሉ… ግን ጆሮ ሆሉ ቢያሳክከውም ሊሰማው የሚገባ አንድ እውነት አለ መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑ፡፡

ይመስላል

 • ይመስላል ብዙ አመት በምድር ላይ ስለቆየን የዘላለሙ መጀመሪያ የራቀ
 • ይመስላል አመጻ በእየስፍራው ስለ በዛ እግዚአብሔር ምድርን የተዋት
 • ይመስላል ምድራዊ አመለካከት የሰማዩን ያሸነፈው
 • ይመስላል የዛሬው መልካችን፣ ገንዘባችን፣ አውቀታችን ነገ እንደምናገኘው
 • ይመስላል ለወንጌል የተሰደዱ ተሸናፊዎች የሆኑ
 • ይመስላል ….

ግና ግን

 • አመጸኛው አመጹን አንድ ቀን ሊያበቃ፣ የክብር ጌታ ሊገለጥ፣ በጎቹ ከፍየሎች ሊለዩ፣ የዘላለሙ መጀመሪያ ሊጀመር ግድ ነው፡፡ ነገሩም ወደ ፍጻሜው እየቸኮለ ነው፡፡

ሃሳቤ እና ልቤ

እዚያው በግርግሩ በሚክሲኮ አደባባይ ይህን አሰብኩ … በቀደም በሸገር 102.1 የሰማሁትን፡፡ ፕሮግራሙ የተላለፈው ለ 2004 ዓ.ም ዋዜማ አከባቢ ነው፡፡ ጋዜጠኛው የተለያዩ የአዲስ አበባ ነዎሪዎችን ስለ 2003 ዓ.ም ጠየቀ… አመቱ እንዴት አለፈ ብሎ፡፡ ሁሉም አንድ አይነት መልስ እንዲመልሱ የታዘዙ ይመስል ሁሉም የመለሱት አንድ አይነት ነበር፡፡ አሉ ኑሮውን አልቻልነውም፣ አሉ እንጀራ በልተን ለማድር ተቸገርን፡፡ ኑሮዎ የሚያንገላታው ህዝብ ከእንግልቱ እስካልወጣ ድረስ መንገድ ላይ እየሄዳ በሃሳብ መዋጡ፣ መንገዱን እረስቶ ሌላ መንገድ ውስጥ መግባቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ እኔን አንድ ሃሳብ ውስጥ ጨመረኝ፡፡ ብዙ ለማግኘት ሰው እየሮጠ፣ የገንዘብ ምንጩን ለማስፋት እየባተለ እያለ እንዲህ ኑሮውን መቋቋም ካቃተው እከሌና እከሊት እንዴት ሊሆኑ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ ጥቂት የማይባሉ አከሌዎችን ከአዲስ አበባ ውስጥ እና ከአዲስ አበባ ወጪ ካሉ ስፍራዎች አሰብኩ፡፡ አሳቤን ገፋሁበትን፣ ወደ ልቤ ይተመስጦ ክፍል ይዤቸው ገባሁ፡፡

አንድ ቀን አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል ፊትለፊት ካሉ የታክሲ ተራዎች መካከል ከአገኘሁት 7ት አመት ያለፈውን አገልጋይ ወዳጄን አገኘሁት፡፡ ይህ አገልጋይ ወንድም ድሮ ሳውቀው ከሚስቱ ጋር ሆኑ ወደ ከተማ በመውጣት ወንጌልን የሚሰብክ ለወንጌል ልቡ የተቃጠለ ሰው ነበር፡፡ ዛሬ ሳገኘው ያልቡ ከእርሱ ጋር ነበር ግን በፈተና ውስጥ እጅግ የተጠመደ ልብ ሆኗል፡፡ ፊቱ ላይ ያየሁት የታሸገ ቁስል ምንነት ስጠይቀው ከቀናት በፊት ወንጌል ሲሰብክ በተወረወረ ድንጋይ እንደተፈነከተ ነገረኝ፡፡ ጥቂት ከተወያየን በኃላ ከፊቱ ላይ ብዙ ነገር አነበብኩ… እርሱም ያነበብኩትን አረጋገጠልኝ… በአገልጋይ ደሞዝ ኑሮን ሊገፋው እንዳልቻለ ነገረኝ… ከ 20 አመት በፊት የተቀበለውን ዲፕሎማ ይዞ ወደ ገብያ ለመግባትም እያሰበ መሆኑን አጫወተኝ፣ ስራ የሚገኝ ከሆነ እንድነግረውም ጠየቀን … እርሱን እያሰብኩ ወደ መኪና ውስጥ ገባሁ፡፡ ከእራሴ ጋር ብዙ አወራሁ የእዚህ ሰው ወደ ስራ መግባት እና አለመግባት፡፡ በከተማ ውስጥ ወንጌልን እየተዘዋወሩ መስበክን ማቆም እና አካውንታንት መሆን፡፡

መኪና ውስጥ ሆኜ ሃሳቤን ቀጠልኩ፣ በሃሳብ ከአዲስ አበባ ወጥቼ ለ ሦስት አመት ወደ ሰራሁበት የእነሞርእና ኤነር ወረዳ ተጎዝኩ፡፡ እነሞር እና ኤነር የሄድኩት ወርልድ ቪዥን በሚባል ድርጅት ተቀጥሬ ነበር፡፡ እዚያ በነበርኩበት ወቅት ከተመለከትኩት ነገሮች አንዱ የአገልጋይ ቤተሰቦች ጉስቁልና ነው፡፡ አንድ ቀን የወረዳው ዋና ከተማ በሆነችው በጉንችሬ ከተማ ውስጥ ከምትገኘው የጉንችሬ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ወንጌላዊ ከሆኑት ከወንጌላዊ ክፍሌ ጋር ስለ አገልጋዮች ሁኔታ ስንጫወት የኑሮው ጉስቁልና በወረዳው ባሉ አገልጋዮች ላይ እየከበደ እንደመጣ አንዳንዶቹም አገልግሎቱን ጥለው ወደ አዲስ አበባ ለንግድ እንዲሁም ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ለመቀጠር እንደሚሄዱ ነገሩኝ፡፡

አኒህ ሁለት አገልጋዮች አይተዋወቁም የአዲስ አበባው ባለ ዲፕሎማ እና የጉንችሬው የሁለተኛ ደረጃ የደረጃ ተማሪ ባለ ሰርተፍኬት፡፡ እኔ ግን አውቃቸዋለሁ፡፡ እኒህ ወዳጆቼን ሁለት ነገሮች አንድ ያደርጋቸዋል ሁለቱም ሥራቸው ወንጌልን ማገልገል ነው፣ ሁለቱም በኑሮው ማእበል እየተንገላቱ ነው፡፡ አንዳንዴም ማእበሉ ገዝፎ ወደ ሌላ ስርአት ውስጥ የሚተፋቸው ይመስላቸዋል፡፡ እም…ከአእምሮ አልፎ ወደ ልብ የሚገባ ትካዜ በብዙ ወንጌላውያን፣ ሚስዮናውያን፣ አባቶች እና እህቶች… ልብ ውስጥ አለ… በእርግጥ መፍትሄ ይሻል…

የተሳፈርኩበት የአራት ኪሎ ታክሲ ፒያሳ ሊደርስ ሲል እንደመባነን ብዬ ከሃሳቤ ተመለስኩ ወዲያው ከፍዬ ወረድኩ እና ወደ ሌላ ታክሲ ገባሁ፣ ጉዞዬ በ ጳውሎስ መስመር ወደ ሚገኘው ቢሮዬ ነው፡፡ በእዚህ መስመር ላይ ከሚጠሩት የመዳረሻ ስሞች መካከል ጳውሎስ እና ፓስተር ይገኙበታል፡፡ ከሁለቱ ስሞች በስተጀርባ ሁለት የወንጌል አገልጋይ የነበሩ፣ አገልግሎታቸውን በድል ጨርሰው ያለፉ ሰዎች አሉ፡፡ እኒህ ስዎች ሳስብ በደስታ አስባቸዋለሁ፡፡ ጳውሎስ … የክርስቶስ አማባሳደር ሆኖ ያለፈው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው፡፡ ፓስተር… በሚስዮናዊው ዶ/ር ላምቤ ሃሳብ አፍለቂነት የተመሰረተው የምርምር ተቋም፡፡ ዶ/ር ላምቤ ከ ፓስተር ተቋም በተጨማሪ ለቀይ መስቀል ወደ ኢትዮጲያ መግባት ምክንያት የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ታዲያ የገባሁበት ታክሲ እኒህን ሁለት ስሞች እየጠራ ሲሄድ የእኒህን ወንድሞቼን ታሪክ አስብ እና በጀግንነታቸው እደሰታለሁ … በሐዋርያው ጳውሎስ እና በሚስዮናዊው ዶ/ር ላምቤ፡፡ እኒህም  ሁለት ሰዎች የሚያመሳስላቸው ሁለት ነገር አለ፡፡ እርሱም የክርስቶስን ወንጌል ለሰዎች ለማድረስ የከፈሉት ዋጋ ሊጠራ የሚችል መሆኑ እና አገልግሎታቸውን በድል ያጠናቀቁ መሆናቸው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ የደረሰበትን መከራ ስናስብ ሰው መሆኑን ልንጠራጠር እንችል ይሆናል፡፡ ግን እንደ እኛው ሰው ነበር፡፡ እስኪ በ ሁለተኛ ቆሮንቶስ የተጠቀሰውን እንመልከት፡፡ 2ቆሮ 11፡23-28

23 በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ።

24 አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ።

25 ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ።

26 ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤

27 በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።

ይላል ጳውሎስ የደረሰበትን ሲዘርዝር፡፡ በእዚህ ሁሉ ድካም ውስጥ ቢያልፍም እጁን ግን አሳልፎ አልሰጠም፡፡ እንደውም …

28 የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። ከድካሙ ባሻገር የሚከብድበት የእግዜአብሔር ቤት ጉዳይ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ጳውሎስ በሕይወቱ የመጨረሻው ምእራፍ የገጠሙት ፈተናዎችም አጅግ ቢበዙም ሩጫውን በድል ጨርሶል፡፡ ለ ጢሞቲዎስ በላከለት ደብዳቤው ላይ ከገለጸው ይህን እንረዳለን፡፡ 2 ጢሞ. 4

6 በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል።

7 መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤

8 ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥

ዶክተር ላምቤም በኢትዮጲያ ውስጥ ወንጌልን ለማድረስ እጅግ እንደተጉ፣ በብዙ መከራ ውስጥም ስለ እርሳቸው የተጻፉ መጽሃፍት እና ሌሎች ጽሁፎች ይጠቅሳሉ፡፡

ዛሬ ሐዋርያው ጳውሎስ የለም፣ ዛሬ ዶ/ር ላምቤ የሉም፣

የዛሬ ባለ አደራ የወንጌል አገልጋዮች የእነሞሩ እና ኤነሩ ወንጌላዊ እና የአዲስ አበባው ባለ ዲፕሎም ሚስዮናዊ ናቸው፡፡ አንዲሁም ጸሃፊው እና አንባቢው፡፡

ከ ፒያሳ ተንስተው በቢሮዬ በር ላይ እያለፉ የሚሰሩት ታክሲዎች ጳውሎስ፣ፓስተር፣ መድሃኒያለም … እያሉ ዛሬም ይጣራሉ፡፡ የአለም መድሃኒት ለመሆን የመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀበልው፣ በመልእክቱ አምነው፣ በእርሱ ብቻ መዳን አለ ብለው በማስተማራቸው የመጣባቸውን መከራ የተቀበሉትን የእምነት አባቶችን ጳውሎስ እና ላምቤን እየጠሩ ይውላሉ፡፡

እናም በታክሲው ውስጥ ገብቼ ሃሳቤን ቀጠልኩ ሦስተኛው ሰው ብቅ አለ ሌላኛው የወንጌል አገልጋይ፡፡ ሌላው በእንሞር እና ኤነር ውስጥ የሚገኝ የቃለ ህይወት ቤተ-ክርስቲያን ወንጌላዊ ይህ ወንጌላዊ ሊጎበኘኝ ሲመጣ ሁሌም ስላደረገው ጫማ ይሳቀቅ ስለነበር አንድ ቀን አንዱን ጫማዬን አንስቼ ሰጠሁት፡፡ ከፊቱ ላይ ከፍተኛ ደስታ አየሱ፣ ከጫማው ሌላ የሰጠሁት ነገር አለ እንዴ ብዬም ተጠራጠርኩ፡፡ ግን አልነበረም፡፡ ልቤ አዘነ፡፡ ምክንያቱም ጥቂት ለማይባሉ ሰዎች በቀላሉ ሊገኝ የሚችል ለእዚህ ሰው ግን ከባድ ነው፡፡ ከእዚያ ቀን በኃላ በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ አግኝቼው አውቃለሁ ያቺን ጫማ አድርጎ አየዋለሁ፣ መቼ ይቀይራት ይሆን…

ይህ ወንጌላዊ ያንን እንደውለታ አድርጎ አዲስ አበባ ከገባሁ በኃላ አንድ ቀን ደወለልኝ … መልእክቱ ከሰል ሊልክልኝ እንዳሰበ እና እንዴት አድርጌ ከሚያመጣለኝ ሰው እንደምቀበል ነበር …

ዶ/ር ለምቤ ሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ በሚያገለግሉበት ጊዜ ከአጠገባቸው ሆኖ በገንዘብ የሚረዳቸው ሰዎች እንደነበሩ እርግጥ ነው፡፡ ጳውሎስ የፊልጲስዮስ ሰዎችን የሚያመሰግንበት አንዱ ነገር፣ ከጉድለታቸው መስጠታቸውን በማሰብ ነበር፡፡

ፊልጲስዩስ 4

15 የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፤

16 በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፥ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና።  በማለት ይጸፍላቸዋል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ አገልግሎቱን የሚደግፉ፣ በገንዘባቸው የሚያገለግሎት እንደነበሩ ሉቃስ ለቲዎፍሎስ እንዲህ ሲል ጽፎለታል

የሄሮድስ አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐናም ሶስናም ብዙዎች ሌሎችም ሆነው በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበር።”  ሉቃስ 8፡3

አዎን በምድራችን ኢትዮጲያ ያለውን የወንጌል እንቅስቃሴ ከማፋጠን አንጻር በአንድነት ልንቆም፣ ልንተባበር ይገባል፡፡ ይህ መተባበር በብዙ መልኩ ይገለጻል ጊዜያችንን ከጊዜ ሌባ በመጠበቅ ስለ አገልጋዮች በመጸለይ፣ ለወንጌል እንቅስቃሴ ከጉድለታችን በመስጠት፣ አገልጋዮቻችንን በማበረታት እንዲሁም በእውቀት በማስታጠቅ፡፡

መቀበል የሚችል ሁሉ፣ መስጠት መቻል ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለመስጠት ደግሞ በስራ ልንበረታ ይገባናል፡፡ ብዙ ለመስራት ጊዜዬን ለመጠቀም እሞክራለሁ፣ ምክንያቱም ብዙ መስጠት ስለሚኖርብኝ፡፡

ቢሮ ደርሼ ከሃሳቤ መለስ ብዬ አብረውኝ ዩንቨርስቲ ይማሩ ከነበሩ ምሩቃን ጋር የጀመርነውን እንቅስቃሴ በተመለከተ በኢ-ሜል የመጡ መልእክቶች እንዳሉ ብዬ kigethiopia@gmail.comን ከፍቼ መልእከቶቼን አነበብኩ፡፡ አመራር ቡድኑ በቀጣይ ስላለው ስብሰባ አጀንዳዎችን ቀረጽኩ፡፡ ወደ facebook በመምጣት ወገኖች ወደ እንቅስቃሴው እንዲመጡ የሚጋብዝ መልእክቱ አስተላለፍኩ፡፡ ወደ www.kigethiopia.webs.com በመሄድ ድህረ ገጻችንን ኪንግደም ኢንቨስትመንት ግሩፕን /KIG/ን ጎበኘሁ፡፡ የእንቅስቃሴያችን አላማ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመሰማራት የአባላትን ገቢ መጨመር እና ከምናገኘው ገቢ ከ 1-10% ለሚስዮናዊ የወንጌል እንቅስቃሴ መስጠት ነው፡፡ ከእኛ ድርጅቶች የሚገኘውን ገንዘብ በመያዝ ከሌሎች ድርጅቶችም እንዲሁም ግለሰቦች የሚገኘውን በመጨመር የወንጌል እንቅስቃሴ ደጀን መሆን ራእይ ያደረገው ድርጅት ሚሽን ፈንድ ኢትዮጲያ የሚሰራውን ስራ ለመመልከት እንደ አጋር ድርጅት ድህረ ገጹን www.missionfund.webs.com ን ጎበኘሁ፡፡

በሚሽን ፈንድ ድህረ-ገጽ ላይ የሰፈረው ብዙ ተስፋ እንዳደርግ አደረገኝ፡፡ ተስፋ ደግሞም የሚሆን፡፡ የወንጌል አገልጋዮች ስለሚበሉት ሆነ ስለሚለብሱት ሳይጨነቁ በወንጌሉ ስራ ላይ የሚያተኩሩበት ስርአት ህይወት ኖሮት ማየት፡፡ ተስፋ ደግሞም የሚሆ፣ በኢትዮጲያ ለሚሆነው የወንጌል እንቅስቃሴ እያንዳንዱ አማኝ ደጀን ሲሆን፡፡ ደጀን ያገኙት አገልጋይ ሚስዮናውያንም በኢትዮጲያ ዙሪያ የከበቡትን ሙስሊም ሀገሮች በወንጌል ብርሃን ሲተዋወቁ፡፡ ተስፋ ደግሞም የሚሆን፣ ክርስቲያኖች በጠንካራ ሰራተኝነታቸው የሚታወቁበት ወቅት ሲመጣ፡፡

እኛ የኪንግደም ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና የሚሽን ፈንድ ኢትዮጲያ አባላት ኢትዮጲያችን አንድም ወንጌል ያልሰማ ሰው እንዳይገኝባት ተስፋ አደረገን፡፡ ሚስዮናውያንን ልንረዳ፣ የሚሽን ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ልንደግፍ፣ ወንጌል ያልገባባቸውን ቦታዎች በማጥናት ከሌሎች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በመሆን ሚስዮናውያንን ለማሰማራት ተስፋ አደረግን፡፡ ደግሞም እንዲሆን አመንን፡፡ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በ 0911-91-33-11 ወይንም በ 0911-75-00-90 ይደውሉ፡፡ ሙሉ ሰላም በኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለ ስለ ቀመስን፣ በእርሱ ሰላም ተባረኩ እንላለን፡፡ ይህ ጽሁፍ የተዘጋጀው በእንቅስቃሴው መሪ በ ሐብታሙ ኪታባ ነው፡፡ ክብር በሰማይ እና በምድር ከጨለማ አውጥቶ ብርሃንን ላሳየን ለታረደው በግ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሆን፡፡ አሜን፡፡

Advertisements

Comments on: "ተስፋ አደረግን፣ እንዲሆንም አመንን" (1)

 1. Habtish please visit this similar blog site of Daniel.

  http://www.danielkibret.com/2010/04/blog-post_29.html

  I found it interesting to read also.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

Tag Cloud

%d bloggers like this: